በ1970ዎቹ-1980ዎቹ በላሊበላ የነበረ ልጅነት

ከኪዳነማርያም ወልደጊዮርጊስ አያሌው ተሞክሮ አንጻር ላሊበላን ስናያት

የተወለድኩት በ1970ዎቹ መባቻ ላይ በላሊበላ ውስጥ ነበር። ቤተሰቦቼ የተዋጣላቸው ነጋዴዎች ነበሩ። ወላጆች ብዙ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ይመላለሱ ስለነበረ በቤተሰብና በትምህርት ረገድ ዘመናዊ የሚባል አመለካከት ነበራቸው። በዚያን ዘመን ላሊበላ የነዋሪዎቹ ቊጥር ከ 4,000 የማይበልጥ ቀደምት በሚባል ስም የምትጠራ ትንሽየ መንደር ነበረች። ዛሬ ግን ያቺ መንደር አድጋ በ4 ቀበሌዎች ተከፋፍላ ከ50,000  በላይ ነዋሪዎች እየኖሩባት ነው። በመንደራችን የነበረው ማኅበራዊ ትስስር በጣም የጠበቀ ነበር። ጎረቤቶቻችን፣ ወዳጆቻችን ወይም ዘመዶቻችን ጥብቅ እርስ በርስ የመታሳሰብና የመታጋገዝ ባህልን ያሳዩን ነበር። ለምሳሌ እናቴ ወደ ገበያ በወጣች ቊጥር ጎረቤቶቻችንን እኛን እንዲይዙ አደራ ብላ ትሄድ ነበር። ሁላችንም በሚገባ እርስ በርስ እንተዋወቅ ነበር። እኔም በበኩሌ ከክፍሌ ተማሪዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነትና ፍቅር ነበረኝ። ዛሬ ላይ የላሊበላ ከተማ ሕዝብ ብዛት በጣም ከመጨመሩ የተነሣ ልክ ትልቅ ከተማ ውስጥ ሲኮን ሁሉንም ሰው ማወቅ እንደማትችል ሆኖ የሚሰማህ ዓይነት ስሜት ሊሰማህ ይችላል።

አንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ከመጀመራቸው በፊት ልጆች በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ የሃይማኖት መጻሕፍትን ማንበብና መረዳትን ይማሩ ነበር። አንዳንድ ሕፃናት በዚያው በሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸው ሲቀጥሉ ሌሎች እንደ እኔ ዓይነቶቹ ደግሞ በወቅቱ በነበሩ «ዘመናዊ» ትምህርት ይሰጡ ወደ ነበሩ ትምህርት ቤቶች በመሄድ ትምህርታችንን ቀጥለናል። ይሁን እንጂ ሁላችንም በስተመጨረሻ በሳምንቱ መጨረሻ የሰንበት ትምህርት ቤት ይባል በነበረው ቦታ የሃይማኖት ትምህርታችንን ለመማር አንድ ላይ እንሰባሰብ ነበር።

አንድ ልጅ ዕድሜው ሰባት ሲሆን በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ወደ የሚሰጠው ደረጃ ይሸጋገር ነበር። ምክንያቱም ሰባት ዓመት ሲሞሉ ሕፃን ልጅ በግዴታ ጾም መጾም የሚጀመርበት ዕድሜ ነው። በዚህም የተነሣ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን መማር እንጀምርለን። ነሐሴ ወር የልጅ ጾም የሚባለውን ጾም እንጾማለን፣ በጾም ጊዜ የሚለበሱ አልባሳትን እንለብሳለን እንዲሁም ቅዳሴ እያስቀደሰን መቁረብ እንጀምራለን። እና ግና ከቆረብን በኋላ ቤት ስንሄድ ወሬ ማውራት አንችልም፣ ከጓዶኞቻችን ጋር መጫወት አንችልም። እንደ አንድ ሕፃን በወቅቱ ብዙውን ጊዜ ከአባቴ ጋር አብሬ ወደ ቤተክርስቲያን እሄድ ነበር። በቅዳሴ ወቅት ታዲያ እግሩ ሥር ድክም ብሎኝ እንቅልፍ ይጥለኝ ነበር።

በየቀኑ የምንሠራቸው ሥራዎች፣ መንገዳችን እና መስተጋብራችን በሙሉ ከቤተክርስቲያን ጋር የተገናኘ ነበር። ለምሳሌ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ የግዴታ በርካታ ቤተክርስቲያኖች እያለፍኩ መሄድ ነበረብኝ። ከሰንበት ትምህርት በኋላ ወይም ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ የቤተክርስቲያናቱ ሕንጻዎች ከዋሻዎቻቸውና ቤተ ሥዕላቶቻቸው ጋር የኛ መጫወቻ ቦታዎች ነበሩ። ቀሳውስቱ «በመላእክት ላይ ነው የምትራገጡት» እያሉ ቢቆጡንም መጨዋታችን አንተውም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያደግነው በጦርነት እንደመሆኑ ጨዋታችንም በአብዛኛው ፍልሚያ ነክ ነበር።  መደባደቢያ ሽመል እንመለምላለን፣ ምሽግ እንሠራለን። እንዋጋለን። አንዳንድ ጊዜ ፍልሚያችን በጎረቤት መንደር ውስጥ ካሉ ልጆች ጋር ነው።የዚያን ጊዜ ከነበረው ፍልሚያ ያተረፍኳቸው አንዳንድ ጠባሳዎች አሁንም ድረስ ሰውነቴ ላይ አሉ። ለከት ስናልፍ እናቶቻችን እኛን ልክ የሚያስገቡበት የራሳቸው ብልሃት ነበራቸው።

ከገዛ ቤተሰብ ውስጥ ካሉ ሴቶች ጋር ከነበረን ግንኙነት ውጪ ከሌሎች ሴት ልጆች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በእጅጉ የተቆጠበ ነበር። በወንድና በሴት መካከል የሚኖረው ግንኙነት የተወሳሰበ ዓይነት ነው። በዚያን ዘመን ላሊበላ ውስጥ የወታደር ካምፖች ነበሩ። ሴት ልጆቻቸው በወታደሮች እንዳይደፈሩ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ከቤት እንዳይወጡ ይከለክሏቸው ነበር። ከቤት መውጣት የግድ ካለባቸው ቡትቶ ለብሰው ነው። መዘነጥ አይችሉም። ልጃገረዶች በቤት ውስጥ በሚሠሩ ሥራዎች እንዲጠመዱ ይደረጋሉ። በኔ ቤተሰብ ውስጥ ግን ወንዶችም ብንሆን የቤት ውስጥ ሥራ የመሥራት ግዴታ ነበረብን። እንጨት እንለቅማለን፣ ውሃ ለማምጣት ወንዝ እንወርዳለን። እንዲህ ሆኖም ግን እንደ ትምህርት ቤት፣ ኩሬ ወይም ወንዝ እና ቤተክርስቲያን የመሳሰሉ ቦታዎች ከመገናኘት አልገደቡንም።

እያንዳንዱ ሃይማኖታዊ በዓል የራሱ የሆነ ሥርዓት ነበረው። እንደ ልጅ መጠን በጣም የምወደው ክብረ በዓል ጥምቀት ነበር። ምክንያቱም የጥምቀት ቀን አዳዲስ ልብስ ይገዛልናል። ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች ይህ ሁሌ የሚያጋጥም ዕድል አይደለም። በዓመት ግፋ ቢል ሁለቴ ወይም ሦስቴ የሚያጋጥም ልዩ ዕድል ነው። እኔ እንኳ በግሌ የማይክል ጃክሰን የሚመስል ልብስና የሮኖልዶ ዓይነት ቁምጣዎች ሲገዙልኝ አሁን ድረስ ፍንትው ብሎ ትዝ ይለኛል። በጳጒሜ የአምስቱ ቀናት ጊዜ ወደ ወንዝ ወርደን እንዘፍናለን፣ እንጨፍራለን፣ እንዋኛለን። አዲሱን ዓመት ለማክበር በቡድን፣ በቡድን ተከፋፍለን በየቤቱ እንዞራለን። ለጎረቤቶቻችን እየዘፈንን ወይም አበባ ስጦታ እየሰጠን እንኳን አደረሳችሁ እንላቸዋለን። እነርሱም በምላሹ ሳንቲም ወይም ሙልሙል ዳቦ ይሰጡናል።

ከሁሉም በዓላት በበለጠ ገና በተለየ ሁኔታ የሚከበር ልዩ በዓል ነበር። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ትግራይን ጨምሮ የተለያዩ የንግሥ ተጓዦች ወደ ከተማችን በእግራቸው ይመጣሉ። እየዘመሩ ሲሄዱ እኛ ደግሞ ከኋላ ኋላቸው እየተከተልን መዝሙራቸውን እንሰማለን። መዝሙሮቻቸው እስካሁን ድረስ በልቤ ውስጥ ተቀርጸው ቀርተዋል። ገና በላሊበላ በትልቅ ደረጃ የሚከበር በዓል ነበር። መዝሙሮቹንና ጭፈራዎቹን ለማየት ከአንዱ ቤተክርስቲያን ወደ ሌላው፣ ከአንዱ የከተማዋ ክፍል ወደ ሌላው እንሮጣለን። በየቤታችን የንግሥ ተጓዦችን ምሳና እራት እንጋብዛለን። ዛሬ ላይ በርካታ ከአዲስ አበባ የሚመጡ የንግሥ ተጓዦች የሚመጡት በአይሮፕላን ነው።

ሃይማኖታዊ በዓላት ወንዶች ልጆች ለልጃገረዶች በግላቸው ያላቸውን ፍቅር መግለጽ የሚችሉበትን ዕድል ይሰጧቸዋል። ጥምቀት ላይ ልጃገረዶች ወደ ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ። እንዲያድሩም ይፈቀድላቸዋል። የቤተሰብ ቁጥጥርን ለመጋፈጥ አቅሙ ያላቸው ተለቅ፣ ተለቅ ያሉት ልጃገረዶች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ድብቅ ፍቅራቸውን ይወጣሉ። በአፈታሪክ እንደሚነገረው በፍቅር የከነፈ ልጅ ፍቅሩን ለመግለጽ የወደዳት ልጅ ላይ ሎሚ ይወረውራል። ልጂቱ እሱ የወረወረውን ሎሚ ካነሣቸውና ካሸተተችው፣ የፍቅር ግብዣውን እንደተቀበለችው ይቆጠራል። በዚያን ዘመን በዚህ መልኩ ነበር ወንድና ሴት ወደ ፍቅር የሚገቡት። ይሁን እንጂ እኅቱ እንዳትነካበት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚያደርግ ወንድሟን ቁጣ በመፍራት እንቅስቃሴያችን ሁሉ በተቻለ መጠን በድብቅ መሆን ነበረበት። የቅድስት ቤተሰብን ወደ ግብፅ ያደረጉትን ስደት በማሰብ ከጥቅምት መባቻ ጀምሮ እስከ ኅዳር መባቻ በሚጾመው በፅጌ ጾም ጊዜ የላሊበላ ወንድ ልጆች በቤተክርስቲያኑ መግቢያ አካባቢ ከፍቅረኞቻቸው ጋር ቀጠሮ ይይዛሉ።

በወርኃ ነሐሴ አንዱ ሳምንት ለልጃገረዶች በተለየ የተሰጠ ሳምንት ነው። ስሙም እሸንዴ ይባላል። በዚህ ሳምንት ሴቶች እንደፈለጉት መልበስ፣ መቆነጃጀት እና ጸጉራቸውን እንደፈለጉት ዘንጠው መሠራት ይችላሉ። ዐሥራ ሦስት፣ ዐሥራ ሦስት ሆነው በቡድን ይደራጁና አንድ የየራሳቸውን መሪ ይመርጣሉ። ይጨፍራሉ፣ ይዘፍናሉ። ሰዉም በአፃፋው የገንዘብ ሽልማት ይሰጣቸዋል። አሸንዴ ዛሬም ድረስ ይከበራል ግን አሁን፣ አሁን ፌስቲቫል ይመስላል።

እነዚህ ሁሉ የልጅትነት ጣፋጭ ትዝታዎቼ ናቸው ይሁን እንጂ ከጦርነት ጋር በተያያዘ በፍርሃት የተሞሉ የልጅነት ዘመኖች ነበሩ።

እኔ የኖርኩባት ላሊበላ ዛሬ ልጆቼ ከሚያውቋት ላሊበላ በጣም የተለየች ነበረች። ዛሬ ላይ ላሊበላ ዘመናዊ የቱሪስት ከተማ ሆናለች። ቋሚ ቅርስ መሆኗ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ ላይ እንደ በፊቱ ወደ ቤተክርስቲያናቱ መሄድ አይቻልም። ጥበቃ አለ። ዙሪያቸው በአጥር ታጥሯል። ሕፃናት እንደ በፊት በዚያ አካባቢ እንዲጫወቱ አይፈቀድላቸውም። የሃይማኖት ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ ሕፃናቱ ዛሬ ላይ የሚሄዱት ወደ መዋለ ሕፃናት ነው። እኛ ልጆች ሆነን ለቤታችን በጣም አስፈላጊ ስለነበረ እንጨት እንለቅምና ውሃ ለማምጣት ወንዝ እንወርድ ነበር።ዛሬ ግን ውሃም መብራትም ቤት ድረስ ገብቷል። በኛ ዘመን ዓለምን የምናውቃት በትምህርት ቤታችን በኩል ብቻ ነበር። የዛሬ ልጆች ግን ከመላው ዓለም ከሚመጡ ቱሪስቶች በሚያገኙት መረጃ መጻዒ ሕይወታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል በቀላሉ ሊገምቱ ይችላሉ።