አዲሽአዴ ድልድይ

ከላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናት አናት ላይ ሕንጻዎቹ ተሰብስበው የሚገኙባቸውን ሁለቱን ቦታዎችን በአንድ በኩል እና እንዲሁም የአዲሽአዴ  ሰፈርን በሌላ በኩል መሀል ለመሀል ለሁለት በመክፈል አዲስ በድንጋይ የተገነባ ድልድይ ተሠርቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። ይህን ግንባታ ማከናወን ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት ታሪካዊ ሕንጻዎቹ ከሚገኙባቸው ጎድጓዳ ቦታዎች አንዱ የላሊበላን ላይኛውና ታችኛውን ክፍል የሚያገናኘውን መተላለፊያ ቦታ ባዶ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ ነው። ይህ ቀደም ሲል ተደፎኖ የነበረውን ጎድጓዳ ቦታ የሞላውን አፈርና ድንጋይ ዝቆ ማውጣት ሥራ በታሪካዊው ቦታ ላይ ያሉትን መተላለፊያዎች ወደ ነባር አገልግሎቶቻቸው የመመለስ ዓላማ ያለው የአርኪዮሎጂና የመሬት ገጽታ ወደ ነበረበት የመመለስ ሥራ አንድ አካል ነው። እነዚህ ሥራዎች የተከናወኑት በአርኪዮሎጂ ባለሙያዎች ቡድን እየተመሩ ሲሆን የሥራዎቹ ዝርዝር ወደፊት በሚወጣው ዜና መጽሔት የሚገለጽ ይሆናል።

ይህ ፕሮጄክት በ 2012 ዓ.ም. ሲጀመር ለአፋጣኝ ቅርስን የመጠበቅ እና የላሊበላን ታሪካዊ ቦታ የማጠናከር ሥራ እንዲያገለግሉ የፈረንሳይ የኢትዮጵያ የጥናት ማዕከል (ሲኤንአርኤስ) አንቷን ጋሪክ የተባሉትን የድንጋይ ቅርጽ ማውጣትና የቅርስ ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያን እና እንዲሁም ስለ ቦታው ጥልቅ ዕውቀት ያላቸውን አቶ ኪዳኔ አያሌውን ሥራውን በበላይነት እንዲመሩ መድቧቸው ነበር። በዚህም አቶ ኪዳኔ አያሌው ባስቀመጡት መስፈርት ላይ በመመርኮዝ ለላሊበላ ታሪካዊ ቦታ ዘላቂ ጥገና ለማድረግና ቅርሶቹን ጠብቆ ለማቆየት በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት 19 የዕደ ጥበብ ባለሙያዎችን (ድንጋይ ቅርጽ ማውጣት ባለሙያዎች፣ ግንበኞች እና አናጢዎች) ተመርጠዋል። አንቷን ጋሪክ ደግሞ እነዚህን ባለሙያዎች የማሠልጠኑን ኃላፊነት ወስደዋል። ሥልጠናው ከበርካታ ሌሎች ነገሮች መካከል በዋንኛነት የድንጋይ ቅርጽ (ስትራክቸር) አወጣጥ የሚያካትት ሥልጠና ሆኖ እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ በመተባበር በርካታ ድልድዮችን ሠርተዋል። አቶ ኪዳኔ አያሌው በበኩላቸው ሥራውን እና አስፈላጊውን ሎጀስቲክ አቅርቦት በማስተባበር፣ ቡድኖቹን በበላይነት በመምራት እንዲሁም በላሊበላና በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግሥትና የሃይማኖት ኃላፊዎችን በየቀኑ በማስተባበር ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

ለሁለት ዓመት ሥልጠናው ከተሰጠ በኋላ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎቹ ራሳቸውን ችለው የአዲሽአዴ ድልድይን ወደ መገንባቱ ሥራ ገብተዋል።

ሙሉ በሙሉ ከዛው በላሊበላ አካባቢ ከተገኙ አለቶች እየተጠረቡ በወጡ ድንጋዮች የተገነባው አዲሱ የአዲሽአዴ ድልድይ ከታች ከወለል ጀምሮ ወደ ላይ ስድስት ሜትር የሚወጣ መሠረት ያለው እና ራሱን በራሱ ደግፎ የሚቆም ሙሉ በሙሉ በድንጋይ የተገነባ ዓምድ አለው። የሚያምሩት የድልድዩ አጥሮች አካባቢውን ከድልድዩ ላይ ቆመው በማየት ለማድነቅ ለሚፈልጉ እግረኞች አጥሩን ተደግፈው ማየት የሚችሉበትን ዕድል ይሰጣቸዋል። አዲስ የተቆፈረው ጎድጓዳ ቦታ፣ ድልድዩ እና እንደ አዲስ የተጠገኑት በዙሪያው የሚገኙ ጎጆ ቤቶች ከቦታው የመሬት አቀማመጥ ጋር ሙሉ በሙሉ ያለምንም እንከን እንዲስማሙ ስለተደረጉ በቦታው ላይ ተጨማሪ ውበትን ፈጥረዋል።

የአዲሽአዴ ድልድይ ሥራ ላይ በከተማዋ የሚኖሩ ሠላሳ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል። እነዚህ ባለሙያዎች ወደፊት የላሊበላ ዘላቂ ጥገና ፕሮጄክት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ናቸው።

ሆኖም ግን በየቀኑ እየተባበሰ በሄደው የጸጥታ ችግር ምክንያት አንቷን ጋሪክ እና አቶ ኪዳኔ አያሌው ለአዲሽ ዐደይ ድልድይ ግንባታ ወደ ላሊበላ እንደፈለጉት እንዳይጓዙ ስላደረጋቸው የዕደ ጥበብ ባለሙያዎቹ ሥራ ችግር አጋጥሞት ነበር።  በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. በከተማዋ ዙሪያ በሚገኙ ቦታዎች ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች እና በአማራ ፋኖ መካከል ከባድ ውጊያዎች ተደርገውበት ነበር። ላሊበላ ወዲያውኑ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከዋለችበት ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ ክፍተኛ ውጥረት ነግሥ ነዋሪዎችን ሲያጨንቅ ከቆየ በኋላ በወርሐ ኅዳር ላይ እጅግ ዘግናኝ ውጊያ በከተማዋ ውስጥ እና በዐብያተ ክርስቲያናቱ አካባቢ ተደርጓል።

ከወርሐ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎቹ ከአዲስ አበባ ከፈረንሳይ የኢትዮጵያ የጥናት ማዕከል ቢሮ በስልክ በሚሰጣቸው መመሪያ እየታገዙ ሥራዎቸውን በመቀጠል የአዲሽአዴ ድልድይን ግንባታ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ችለዋል። የቴክኒክ ምክር፣ የተሠሩ ሥራዎችን ጥራት ማረጋገጥ፣ የፋይናንስ እና የሎጀስቲክ ድጋፍ በሙሉ ይሰጥ የነበረው በስልክ ነበር። ባለሙያዎቹ በተወሰነ መልኩ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት በሚችሉበት ወቅት ላሊበላ የሚገኘው የዕደ ጥበብ ባለሙያ ቡድኑ ሱፐርቫይዘሮች የሆኑት አምባቸው ተገን እና ሲሳይ መቆያ የሥራ ሪፖርት፣ ፎቶግራፎችን ይልኩ ነበር ወይም ፕላኖችና ቴክኒካል ምክሮችን ይጠይቁ ነበር።

የአዲሽአዴ ድልድይ የአካባቢው አገር በቀል የቅርስ ጥበቃ ጥበብ፣ የሳይንሳዊ ትብብር እና የላሊበላ ዕደጥበብ ባለሙያዎች ፅናትና አይበገሬነት ታሪክ ነው።